በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትን ዓላማ ያደረገ የፕሮጀክት ሰልጣኝ አትሌቶች ውድድር እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትን ዓላማ ያደረገ የፕሮጀክት ሰልጣኝ አትሌቶች ውድድር እየተካሄደ ነው
መቀሌ ፤ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በአትሌቲክስ ፕሮጀክት የታቀፉ ሰልጣኝ ታዳጊ አትሌቶች የብቃት ምዘና ውድድር ዛሬ ተጀመረ።
ዛሬ የተጀመረው የ17 ዓመት ታዳጊዎች የአትሌቲክስ የብቃት ምዘና ውድድርም ለቀጣዮቹ ሦስት ቀናት እንደሚካሄድም የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የስፖርት ኮሚሽን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳነ ተክለ ሀይማኖት እንደገለፁት፤ በውድድሩም ከክልሉ ስምንት ወረዳዎች የተውጣጡ 420 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን 120 የሚሆኑት ሴት አትሌቶች ናቸው።
በዚህ ውድድር ጥሩ ብቃት ያሳዩ ታዳጊ አትሌቶችን በመመልመል ክልሉን ብሎም አገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን የመለየት ተግባር እንደሚከናወን ገልፀዋል።
ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ውድድር በ100 ሜትር፣ በ800 መቶ፤ በ1 ሺህ 500 እና በ2 ሺህ ሜትር ርቀቶች የብቃት መመዘኛ ፉክክር እንደሚከናወን የገለፁት ደግሞ በክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአትለቲክስ ውድድር ባለሙያ ጌታቸው ማሞ ናቸው።
የብቃት ምዘና ውድድር ለማድረግ በስፍራው ከተገኙት አትሌት ፍረወይኒ ተስፋይና ወይናረግ ካህሱ በ2 ሺህ ሜትር ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን አገርን ለመወከል እንዳቀዱም ተናግረዋል።
አትሌት ኮኮብ ገብረ መድህንና ዳኒኤል ተክላይ በበኩላቸው በ1 ሺህ 500 ሜትር በመወዳደር ቀጣይ ጉዟቸውን ብሩህ ለማድረግ ማሰባቸውን ገልፀዋል።
በተያያዘም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የላካቸው የልምምድና የመወዳደሪያ የስፖርት ትጥቆች ርክክብ ተካሄዶ ለፕሮጀክት ሰልጣኞቹ እንዲከፋፈል ተደርጓል።
በወቅቱም ፌዴሬሽኑ መሰል የስፖርት ትጥቅ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጠይቋል።