የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገርም አልፎ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው -ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገርም አልፎ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው -ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 14/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገርም አልፎ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስቴር ነገ የሚከበረውን 117 ኛውን የመከላከያ ቀን አስመልክቶ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎችና ዲፕሎማቶች ገለጻ አድርጓል።
በመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገርም አልፎ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ሰራዊቱ የሀገሩን ዳር ድንበርና የህዝቡን ደህንነት በማስጠበቅ የጸናች ሀገርን ማስቀጠል ችሏል ሲሉ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና ሌሎችም አገራት የላቀ ሚና ሲወጣ መቆየቱንና አሁንም እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ህልውና እንዲሁም አህጉራዊ ሰላም የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለመድረኩ ታዳሚያን ኢትዮጵያ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ፣በዘመናት የመንግስታት መለዋወጥና የትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ የጸናች ሀገር ለማስቀጠል የመጣበትን መንገድ እና አሁን የደረሰበትን ተቋማዊ እድገት በተመለከተ ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል።