ቀጥታ፡

በደብረ ብርሀን ዘመናዊ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎትን ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ደብረብርሀን፤ ጥቅምት 14/ 2017(ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ከተማ የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የሚያግዝ ዘመናዊ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

ከተማ አስተዳደሩ ከፊቤላ ኢንዱስትሪያል ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደብረብርሀን መኪና መገጣጠሚያ ፋበሪካ የገዛቸውን ዘመናዊ ሁለት የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ዛሬ ተረክቧል።


 

በዚህ ወቅት የደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንዳሉት፤ አስተዳደሩ በከተማ የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት የሚያግዙ ሁለት የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች በመግዛት ለአገልግሎት እያመቻቸ ነው።

ይህም ችግርን በራስ አቅም የመፍታት ባህልን የሚያሳድግ ነው ብለዋል ።

አውቶቡሶቹ በመንግስት የስራ ሰዓት መግቢያና መውጫ ለመንግስት ሰራተኞች፤ በቀሪው ሰዓት ለነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

መንግስት እያካሄደ ያለው ሰው ተኮር ልማት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በአውቶቡሶቹ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀለፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል ።

የህዝቡን ችግር ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው ተግባራት ለሌሎችም አርአያነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የፊቤላ ኢንዱስትሪያል ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደብረብርሀን መኪና መገጣጠሚያ ፋበሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ አህመድ ፤ አውቶቡሶቹ የአካባቢን ብክለት የማያደርሱ በኤሌትሪክ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፋብሪካው አዳዲስ ቴክኖለጂዎችን ተጠቅሞ ያመረታቸው ዘመናዊ አውቶቢሶችና ሌሎች የጭነት ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ለሀገር ውስጥ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን አብራርተዋል።

ከደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች መካከል አቶ አሳምነው ወልደተሳይ በሰጡት አስተያየት አውቶቡሶቹ ለሰራተኛው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የጎላ ሚና እንደሚኖቸው ተናግረዋል።

ወይዘሮ ነዋይ ሸንቁጤ በበኩላቸው፤ አውቶቡሶቹ የትራንስፖርት ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚያግዛቸው አመልክተው፤ የተሽከርካሪዎቹን ደህንነት በመጠበቅ አግባቡ ለመጠቀም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም