በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራት ለውጥ እያመጡ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራት ለውጥ እያመጡ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
ጅማ ፤ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራት ለውጥ እያመጡ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ቡድን ዛሬ በጅማ ዞን በጎማ እና ሊሙ ኮሳ ወረዳዎች የሚገኙ የግብርና ስራዎችን እየጎበኘ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ የግብርና ልማትን ለመተግበር እየተሰራ ነው።
አርሶ አደሩን በተለያዩ የስልጠናና የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በመደገፍ ምርታማነትን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም የክልሉ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የእያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ለውጥ እያመጡ መሆኑን አስረድተው በጅማ እና በአጎራባች ዞኖች የተገኘው ውጤት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከጎበኟቸው ቦታዎች መካከል በሊሙ ኮሳ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው ከብት በማድለብ ስራ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ይገኙበታል።
ወጣቶች በተማሩት ሞያ በመደራጀት መሰማራታቸው ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው ሲሉ ለሌሎች ወጣቶችም አርአያ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የእነዚህን ወጣቶች ልምድ በመከተል በርካታ ወጣቶች ከጠባቂነት በመላቀቅ ራሳቸውን እና ሀገራቸውን መለወጥ ይችላሉ ብለዋል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው በዞኑ በግብርና ልማት ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑንና በዞኑ የጉማይ እና የጎማ ወረዳዎች በቡናና በፍራፍሬ ምርት የሚታወቁ መሆኑን ገልፀው በዞኑ በርካታ የግብርና ኢኒሺዬቲቮች እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ፕሬዚዳንት የተመራው የመስክ ስራ ምልከታ ቡድን በነገው እለትም በሌሎች ወረዳዎች የተሰሩ የግብርና ልማት ስራዎችን ይጎበኛል ተብሎም ይጠበቃል።
ዞኑ በቡናና በፍራፍሬ፣ በበጋ መስኖ ስንዴና በሩዝ ብሎም የተለያዩ የግብርና ኢኒሼቲቮችን በመተግበር የተሻለ አፈጻጸም እንዳለውም ተጠቁሟል።