ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ቅርሶችን በመጠበቅና በማልማት ለአገር ዕድገት እንዲውሉ በማድረግ ላይ መሆኑን አመለከተ

ድሬዳዋ ፤ ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፡- ቅርሶችን በመጠበቅና በማልማት ለአገር ዕድገት እንዲውሉ በማድረግ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን  አመለከተ።

በባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይረክተር ወይዘሮ ህይወት ሐይሉ የተመራው የባለስልጣኑ አመራር ቡድን 128 ዓመታት ያስቆጠረውን እና በ13 ሚሊዮን ብር ጥገና እየተከናወነለት የሚገኘውን  የድሬዳዋ ባቡር ጣቢያን ተመልክተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ከጉብኝቱ በኋላ እየተጠገነ ስላለው ቅርስ ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እና ከአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት አመራር አካላት ጋር ተወያይተዋል።

ወይዘሮ ህይወት በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ የአገራችንን ቅርሶች በመጠበቅና በማልማት ሃብቶቹ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ እየሰራ ነው።

በ13 ሚሊዮን ብር ወጪ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ጥገና እየተከናወነለት የሚገኘው የድሬዳዋ የባቡር ጣቢያ አንዱ መገለጫ መሆኑን ለአብነት በማንሳት።

እንደ ወይዘሮ ህይወት ገለፃ  የተርሚናሉ ጥገና በድሬዳዋ ከተጀመረው የኮሪደር ልማት ጋር ተጣጥሞ መካሄዱ የቅርሱን ተፈላጊነትና ቀጣይ  ጠቀሜታዎች በከፍተኛ ደረጃ  ያሳድገዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሐርቢ ቡህ በበኩላቸው 128 ዓመታት ያስቆጠረው የድሬዳዋ ምድር ባቡር ተርሚናል ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በጥሩ ሁኔታ እየተጠገነ መሆኑን ገልጸዋል።

የተርሚናሉ ደረጃውን ጠብቆ መጠገን  ጣቢያው እና በውስጡ የሚገኙት ዘመን የተሻገሩ ቤተሙከራዎች ለአስተዳደሩ ዕድገት እያበረከቱ የሚገኙ አስተዋፅኦ ይበለጥ እንዲጠናከር ያስችላል ብለዋል።

የድሬዳዋ ባቡር ጣቢያ ተርሚናል የቅርስ ጥገና ስራ ከሶስት ወራት በኋላ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ሚካኤል ናቸው።

የጥገና ስራው የኮሪደር ልማቱ ቅርሶቹን ይበልጥ ይፋ እያወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የቱሪስቶችና የነዋሪዎች ተመራጭ መዳረሻ ማዕከል እንደሚያደርገው በመግለፅ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም