ቀጥታ፡

በመዲናዋ ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ከነገ ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት በኦንላይን ምዝገባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በዘንድሮው ዓመት ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ከነገ ጥቅምት 15ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት በኦንላይን ምዝገባ እንደሚያካሄድ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ። 

በቢሮው በ2017 የትምህርት ዘመን ወደቴክኒክና ሙያ የሚገቡ ተማሪዎችን ቅበላ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው የውጤት ተኮር ስልጠና እና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አበራ ብሩ እንዳሉት በከተማዋ በ2016 አገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ 50ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 23 ሺህ 835 በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተመድበዋል።

ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ 4 ሺህ145 ተማሪዎች በደረጃ አምስት፣ 15 ሺህ 545 ተማሪዎች በደረጃ አራትና ሶስት እንዲሁም 4 ሺህ 145 ተማሪዎቸ ደግሞ በደረጃ ሁለት ስልጠናዎችን እንደሚከታተሉ ተናግረዋል።     

ምዝገባው የሚከናወነው በኦንላይን መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በ14ቱ የመንግስት ኮሌጆች በተዘጋጀው ሊንክ በመግባት ከነገ ጀምሮ ባሉት 10 ቀናት ምዝገባ ማከናወን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኞች ምዝገባቸውን ሲያካሂዱ የሚደርሳቸው አጭር ኮድ እንዳለም አስረድተዋል።   

የከተማዋን መልማት ፀጋ ታሳቢ ተደርገው ለሚሰጡት 129 ሙያዊ ስልጠናዎች አስፈላጊ የሆኑ የግብአት፣ የማሰልጠኛ ቦታና የሰው ኃይል ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በከተማዋ በተያዘው ዓመት ለ300 ሺህ ወጣቶችና ሴቶች በተለያዩ ሙያዎች አጫጭር ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቅሰው በመጀመሪያው ሩብ አመት 24 ሺህ ወጣቶች መሰልጠናቸውን አብራርተዋል።

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም