በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ከወጪ ንግድ(ኤክስፖርት) ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) አፈጻጸምን ከላኪዎች ጋር መገምገማቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።


 

አፈጻጸሙ በምርት ጭማሪም ሆነ በውጭ ምንዛሪ ዕድገት ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን አመልክተዋል።

ይህም ከእቅዱ 132 በመቶ መሳካቱንና ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻርም ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጭማሪ እንዳለው ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን በማላቅ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ከዘርፉ ተዋናዮች እና ከላኪዎች ጋር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም