ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ በ2028 ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተመላከተ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2028 ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት አመላከተ።

ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞባይል ኔትዎርክ ኦፕሬተሮችን የሚወክል ተቋም ሲሆን፣ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የሞባይል ኦፕሬተሮች እና መለስተኛ ኦፕሬተሮችን ጨምሮ 26 የቦርድ አባላት ያሉት ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡

በዛሬው እለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ በጋራ በመሆን የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚን በተመለከተ የፓናል ውይይት እያካሄዱ ነው፡፡

በፓናል ውይይቱ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩንና "የጂ.ኤስ.ኤም.ኤ" ዓለም አቀፍ ሬጉላቶሪ ኦፊሰር ጆን ጊዩስቲ ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመድረኩም በኢትዮጵያ ዲጂታል ሽግግር ላይ ትኩረት ያደረገ ሪፖርት ይፋ ሆኗል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የቴሌኮም ማሻሻያ እና የሞባይል ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንቶች በግብርና፣ በአምራች ዘርፍ፣ በሕዝብ አገልግሎትና በሌሎች ዘርፎች ፈጣን እድገት እያመጡ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2028 ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 1 ነጥብ 3 ትሪሊን ብር አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው፡፡

ከ1 ሚሊየን በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥርና ለመንግሥት ተጨማሪ 57 ቢሊየን ብር ከታክስ ገቢ እንደሚያስገኝም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም