ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ቻይና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያና ቻይና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከቻይና የትምህርት ምክትል ሚኒስትር እና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ ዉ ያን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በትምህርትና ሥልጠናው ዘርፍ ያለውን የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ እና ቻይና በትምህርትና ስልጠናው ዘርፍ የረዥም ጊዜ ትብብር እንዳላቸው ጠቅሰው አሁን ላይ በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴክኒክና ሙያ ልህቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ያለው የቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት በቻይና መንግስት ድጋፍ መሰራቱን አመልክተዋል።

የቻይና የትምህርት ምክትል ሚኒስትርና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ ዉ ያን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረችውን ሪፎርም አድንቀው በሁለቱ ሀገራት መካከል በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የነበረውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት ዘርፉን በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ማጠናከር እና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዘርፉን ሪፎርም መደገፍ የሚያስችሉ ተጨማሪ አዳዲስ የትብብር መስኮች ተለይተው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እና የቻይና የትምህርት ምክትል ሚኒስትርና የኮሙኒስት ፓርቲው ተወካይ ዉ ያን በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የሚገኘውን የሉባን ወርክሾፕ ጎብኝተዋል።

በተጨማሪም የቴክኒክ እና ሙያ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) ከቲያንጅን ቴክኖሎጂና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዣንግ ጂንጋንግ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም