የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
መቀሌ 70 እንደርታ ከድሬዳዋ ከተማ ከ10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው መቀሌ 70 እንደርታ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል። መቀሌ 70 እንደርታ በአምስት ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በሶስቱ ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
በይታገሱ እንዳለ የሚሰለጥነው ድሬዳዋ ከተማ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ከምሽቱ 1 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋሲል ከነማ ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል።
በሁለቱ ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር አራት ጎሎችን አስተናግዷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በሶስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል።
በውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ በስድስት ነጥብ አምስትኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የሊጉ መርሃ ግብር ነገ ቀጥሎ ሲውል ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት እንዲሁም ሃዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆዩ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።
ሲዳማ ቡና በዘጠኝ ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ ቻርልስ ሙሲጌ በአራት ግቦች ይመራል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ኪቲካ ጅማ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፍጹም ጥላሁን፣ የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ እና የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ በተመሳሳይ ሶስት ግቦች ይከተላሉ።