ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ትልቅ አቅም አላት - የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ማክሊን ኮርቴዝ ሌትሺዊቲ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ትልቅ አቅም አላት - የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ማክሊን ኮርቴዝ ሌትሺዊቲ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2029 የሚካሄደውን 37ኛው የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ አቅም እንዳላት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞው የቦትስዋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ማክሊን ኮርቴዝ ሌትሺዊቲ ገለጹ።
46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) የኢትዮጵያን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ እንዲቀበል እና እንዲያጸድቅ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞው የቦትስዋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ማክሊን ኮርቴዝ ሌትሺዊቲ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ለጉባዔው ልዑካን ያሳየውን እንግዳ ተቀባይነት አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት በጎ እሳቤ እና ቁርጠኝነት እንዳለው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2029 የሚካሄደውን 37ኛው የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ አቅም እንዳላትም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ዋንጫ ማስተናገድ ጥያቄው በካፍ አሰራር የሚታይ ቢሆንም ኢትዮጵያ አህጉራዊውን ሁነት የማዘጋጀት የቅድሚያ እድል እንደምታገኝ ጥርጥር የለኝም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም መስክ ለአህጉራዊው ልማት በቁርጠኝነት የምትሰራ እውነተኛ አፍሪካዊ አገር መሆኗንም ነው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል የገለጹት።
የደቡብ ሱዳን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ምክትል ፕሬዝዳንት አጉስቲኖ ማዱት ፓሬክ በበኩላቸው አዲስ አበባን የአፍሪካ ቤት ሲሉ ገልጸዋታል።
ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ሆና ብትመረጥ የደስታ ስሜት እንደሚፈጥርባቸውና ውድድሩን ማዘጋጀቷ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እና ለካፍ ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት (በቀድሞው ስያሜው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት ለውጦች ያደነቁት ማዱት ፓሬክ ሀገሪቷ በእግር ኳስ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እና አንድነትን መፍጠር እንደምትችልም ገልጸዋል።