ቀጥታ፡

በጥጥ ልማት ረገድ ያሉ ተግዳሮቶችን ለማቃለል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ -ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን

ሰመራ ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፦ በጥጥ ልማት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለማቃለል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንደሚጠናከሩ የአፋር ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን ገለፁ።

የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተካሄዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን እንደገለፁት፤ በጥጥ ልማት ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶችን የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለማቃለል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ።

በተለይም ከፋይናንስ አገልግሎት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዘርፉ የሚጠይቀውን አሰራር ተከትሎ እንደሚከናወን ነው ያብራሩት።

በዘርፉ እየታየ ያለውን ጉድለት ለማሟላት የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የክልሉ መንግስት ባለሃብቱ እየተበረታታ የሚሄድበት አሰራር እያጠናከረና ችግሮችን እየፈታ እንደሚሄድ ገልፀዋል። 

ምርቱ እንዳይበላሽና የጥራት ደረጃው እንዳይቀንስ የምርት አሰባሰብ ሂደት ላይ ያጋጠመውን የሰው ሃይል እጥረት ለማቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ ጥጥ አልሚዎች፣ መዳመጫዎችና ላኪዎች ማህበር ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ መሐመድ ኡዳ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት፤ ለዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት እና የብድር አገልግሎት በማመቻቸት ማጠናከር ይገባል።

በተጨማሪም ያለውን የሰው ኃይል እጥረት በማቃለል የተመረተው ምርት ጥራቱን ሳይቀንስ ሊሰበሰብ እንደሚገባም አክለዋል። 

የዘርፉን የፋይናንስ አማራጮች ተግዳሮት ለማቃለል በተዘጋጀው መድረክ ላይ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም