በአፍሪካ ቀንድ የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ የአካባቢው አገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ቀንድ የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ የአካባቢው አገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፡- በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የጋራ ልማት እንዲረጋገጥ የቀጣናው አገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላከተ።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ግንኙነቷ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ነው።
ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ የአካባቢውን አገራት ሉዓላዊነት ባከበረ አካሄድ፣ ለቀጣናው ሰላምና ልማት በቁርጠኝነት በትብብር እየሰራች መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህ ማዕቀፍ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን ለመመለስና በቀጣናው የጋራ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ከሶማሊላንድ ጋር ሥምምነት መድረሷን ነው ያስረዱት።
ይህም የኢትዮጵያ አካሄድ ምንም እንኳን በርካታ አዎንታዊ ጎኖች ቢኖሩትም በአንዳንድ አካላት ዘንድ በበጎ አለመታየቱ የሚያስገርም መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም በሶማሊያ መንግሥት በኩል የታየው አሉታዊ ምላሽ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የዋለችውን ውለታ ከግምት ያላስገባና ለቀጣናው የጋራ ልማት ረብ የሌለው መሆኑን ገልፀዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ታሪካዊ ጠላት ከሆኑ ኃይላት ጋር በማበር ያሳየው ያልተገባ ተግባርም ተቀባይነት የሌለው አካሄድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም አካሄድ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የሶማሊያ ሕዝብ ሁነቱን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ጭምር በመውጣት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ማስገደዱን አስረድተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የጂኦ-ፖለቲካው መልክ እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ኃይሎች ይህንን ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ከመደገፍ ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይልቁንም በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የጋራ ልማት እንዲረጋገጥ የቀጣናው አገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁሩ ተናግረዋል።