የአፍሪካ አዳራሽ በአዲስ አበባ ዘመናዊ ከተሜነት ታሪክ ያለው ሥፍራ - በኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎች አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አዳራሽ በአዲስ አበባ ዘመናዊ ከተሜነት ታሪክ ያለው ሥፍራ - በኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎች አንደበት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፡- ከሰሞኑ ታድሶ የተመረቀው በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሥር የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ በአዲስ አበባን ዘመናዊ ከተሜነት ታሪክ ምን አይነት ሥፍራ እንዳለው የኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎች አብራርተውታል።
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ አንጡራ ኃብት አስገንብተው ለአፍሪካዊያን በሥጦታ ያበረከቱት ታሪካዊ ቅርስ ነው በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሥር የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ።
የአፍሪካ አዳራሽ ከተገነባ 61 ዓመታት በኋላ በመንግሥታቱ ድርጅት ድጋፍ ከሰሞኑ ታድሶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ና በተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ መመረቁ ይታወቃል።
በዛሬው ዕለትም በኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበርና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሸን የተዘጋጀ የአፍሪካ አዳራሽ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ኪነ-ሕንጻ ግንባታ ታሪክ የነበረውን ሚና የተመለከተ የፓናል ውይይት ተደርጓል።
በፓናል ውይይቱ ላይ እንደተገለጸው የአፍሪካ አዳራሽ ከአዳራሽነት ባሻገር ለአዲስ አበባን ዘመናዊ ከተሜነት ታሪክ ውስጥ መልከ ብዙ አበርክቶ አድርጓል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንጻ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪው አርክቴክት ዳዊት በንቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ አዳራሽ ለዛሬዋ አዲስ አበባ ማንነትና መልክ መሰረት ጥሏል።
በዘመናዊ ኪነ ሕንጻዎች ዙሪያ ጥልቅ ምርምር ያደረጉት አርክቴክት ዳዊት እንደሚሉት ከአፍሪካ አዳራሽ በፊት ዓለም አቀፍ ስብሰባ ማስተናገድ ቀርቶ ሌሎች አነስተኛ ግልጋሎቶች የሚውል ሕንጻዎች አልነበሩም።
አዲስ አበባን በብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን መቀመጫ እንድትሆን ሲወሰን የኮሚሽኑ ስብሰባዎችን የሚያስተናግዱ ህንጻዎች ባለመኖሩ በጠላት ወረራ ዘመን በተሰሩ የቀድሞ መከላከያ ሚኒስቴርና በንግድ ሥራ ኮሌጅ አዳራሾች እንደተደረጉ ያነሳሉ።
በዚህም የአፍሪካ አዳራሽ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1961 የኮሚሽኑን ስብሰባ ለማስተናገድ በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም መሰል ብርቱ ሰዎች ትጋት ለ24 ሰዓት እየተሰራ በ18 ወራት ብቻ ተገንብቶ ተጠናቋል።
ይህ ታሪካዊ አዳራሽ በአጼ ኃይለሥላሴና በዲፕሎማቶቻቸው ብርቱ ትግል 32 የአፍሪካ መሪዎች በፈረንጆቹ 1963 አዲስ አበባ ተሰባስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረቻ ቻርተር የፈረሙበት ቦታም ሆኗል።
የአፍሪካ አዳራሽ ለስብሰባ ቢያስተናግድም ዳሩ የገበያ አዳራሾች፣ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲሁም መሰረተ ልማቶች እንዳልተሟሉም ይናገራሉ።
በዚህም የአፍሪካ አዳራሽ መገንባት የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲገነባ፣ ከቦሌ ወደ ቤተ-መንግሥት የሚያመጣው የአፍሪካ ጎዳና እንዲገነባ አድርጓል።
የአፍሪካ አዳራሽን ጨምሮ ለአፍሪካዊያን የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማሟላቷንና ለአፍሪካ አንድነት የተጫወተችው ሚና አፍሪካዊያን ኢትዮጵያ ቤታችን እንዲሉ አድርጓቸዋልም ይላሉ።
አፍሪካ አዳራሽ የሒልተን፣ ግዮንና ኢትዮጵያ ሆቴሎች እንዲገነቡ፣ ፊንፊኔ ሕንፃ፣ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ በአዲስ እንዲገነባ፣ መስቀል ደመራ ከአራዳ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲዞር ተደርጓል።
በአጠቃላይ የአፍሪካ አዳራሽ መገንባቱ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ኪነ-ሕንጻ ግንባታ ብሎም በአዲስ አበባ ዘመናዊ ከተሜነት በአጭር ጊዜ እንዲያብብ ማድረጉን ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኃብታሙ ጌታቻው በበኩላቸው፤ የአፍሪካ አዳራሽ ከአዳራሽነቱ ባሻገር የኪነ-ሕንጻ ታሪኩ ዕድሳት እንዲደረግለት ማድረጉን ይገልጻሉ።
ታሪካዊው የአፍሪካ አዳራሽ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለመላው አፍሪካ ታሪክ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካዊነት መጎልበት የነበራትን ፈር ቀዳጅ ሚና የሚዘከር ትልቅ አሻራ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በኪነ-ሕንጻ ውበቱና እጅግ በተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የመሥታወት ስዕላት ያሸበረቀው የአፍሪካ አዳራሽ መታደሱ አንድምታው ብዙ ነው።
የትናንቱን የአፍሪካ ታሪክ ለመዘከርና ለተተኪው ትውልድ ለማስተማር ብሎም ለቱሪስት ክፍት በመደረጉም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲያበርክት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።
የአፍሪካ አዳራሽን መሰል የአዲስ አበባ ነባር ቅርሶችን በቅጡ ማጥናት፣ ማደስና መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበርም ለጥንታዊ ሕንጻዎች ብቻ ሳይሆን ድኅረ 1960ዎቹ የተገነቡ ኪነ ሕንፃዎች እንደ ቅርስ እንዲጠበቁ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።