ቀጥታ፡

ዘመናዊ የሥነ-ምድር ካርታ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017 (ኢዜአ)፡- በቴክኖሎጂ ታግዞና አዳዲስ የሥነ-ምድር ኃብቶችን አካቶ የያዘ ዘመናዊ የሥነ-ምድር ካርታ ተዘጋጀ። 

ረቂቅ ካርታው በኢትዮጵያ ያሉትን የዓለት ዓይነቶች ከእነዕድሜያቸው እንዲሁም የከርሰ-ምድር ውኃ ሊገኝባቸው የሚችሉ ሥፍራዎችን ያመላክታል ተብሏል። 

ረቂቅ ካርታው በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በቼክ ሪፐብሊክ መንግሥትና በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የጂኦሎጂ ተመራማሪዎች በትብብር በጋራ ተዘጋጅቷል።  

ረቂቅ ካርታውን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ እየጨመረ ያለውን የሕዝብ ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የውኃ አጠቃቀም ለመፍጠር ያሉትን የከርሰ-ምድር ውኃ ኃብቶች በአግባቡ ማወቅ ይገባል።

በተለይም የተፈጥሮ ኃብቱ አላቂ እንደመሆኑ አማራጭ የከርሰ-ምድር ኃብቶችን መለየትና መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የተፈጥሮ ኃብቶቹን የሚገኝበት ሥፍራ ማወቅ ተገቢ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ኃብት በአግባቡ በመጠቀም ዜጎቿን ከድኅነት ለማውጣት ጥረት እያደረገች መሆኑን ጠቅሰው፤ ካርታው ታትሞ ከመውጣቱ በፊት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጂኦሎጂ ተመራማሪው ለታ አለማየሁ (ዶ/ር) ካርታው በኢትዮጵያ ያሉትን የዓለት ዓይነቶች ከእነዕድሜያቸው እንዲሁም የከርሰ-ምድር ውኃ ሊገኝባቸው የሚችሉ ሥፍራዎችን መያዙንም ተናግረዋል። 


 

በኢትዮጵያ የከርሰ-ምድር ውኃን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ ኃብቶች ያሉበትን ሥፍራዎች በአግባቡ ማወቅና መለየት ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች ብለዋል።


 

በተለይም በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የጂኦሎጂና የኃይድሮሎጂ አቅም በመጠቀም የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እየተሰራ ያለው ሥራ ለማስቀጠል ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት። 

የኃይድሮጂኦሎጂ ጥናት ለኢትዮጵያ ቀጣይ ብልጽግና ወሳኝ ሚና ይጫወታል ያሉት አምባሳደሩ፤ በተለይም የከርሰ-ምድር ውኃ ኃብትን በአግባቡ ለመጠበቅና ለመጠቀም ያለው ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራ እየሰጠ ያለውን ትኩረት አድንቀው፤ ለዚህ ሥራ ውጤታማነት መንግሥታቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ቀደም ሲል ሀገር አቀፍ የሥነ-ምድር ካርታ የተዘጋጀው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1996 ሲሆን ዛሬ ለውይይት የቀረበው በአዲስ መልክ ተሻሽሎ ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም