የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ የተፋሰሱን አገራት ፍትሃዊ የውኃ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ የተፋሰሱን አገራት ፍትሃዊ የውኃ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017 (ኢዜአ)፡- የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ተፈፃሚ መሆኑን የተፋሰሱን አገራት ፍትሃዊ የውኃ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የውኃ ኃብት ተመራማሪና ባለሙያው ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ተናገሩ።
የስምምነት ማዕቀፉ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግን መርሆዎችን መሰረት ያደረገ፣ ፍትኃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ማስፈን፣ ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከር እንዲሁም ጉልህ ጉዳትን ማስቀረት ነው።
በዚህም መሰረት እኤአ በ2010 የስምምነት ሰነዱ ለፊርማ ክፍት የተደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ዩጋንዳ ፈርመው በመቀጠልም ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ፈርመውታል።
በዚህም መሰረት የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ማእቀፍ ከጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የውኃ ኃብት ተመራማሪና ባለሙያው ፈቅ አሕመድ ነጋሽ፤ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት የቅኝ ግዛት ስምምነትን የሻረና ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የቅኝ ግዛት ሥምምነቱ የውኃ አመንጪ አገራትን ታዛቢ ያደረገ፣ በውሃው ምንጭነት ምንም አስተዋጽኦ የሌላቸውን አገራት ፍትሃዊነት በጎደለው መልኩ ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል።
በመሆኑም የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሥምምነት የተፋሰሱን አገራት ፍትሃዊ የውኃ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ከብዙ ጥረት በኋላ ወደ ተፈፃሚነት የገባው የትብብር ማዕቀፉ የተፋሰሱን አገራት የውሃ አጠቃቀም ፍትሃዊ የሚያደርግና የሚከናወኑ ስራዎችንም የሕግ ከለላ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።
የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን በሕግ እንዲቋቋም ማስቻሉም ለተፋሰሱ አገራት ትልቅ እምርታ ሆኗል ነው ያሉት።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሥምምነትን ያጸደቁ አገራት በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና በኃብት አጠቃቀም ዙሪያ በትብብር እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።