በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፡- በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛንያና ደቡብ ሱዳን ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት 6 ሺ 456 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለጎረቤት ሀገራት ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር 36 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ለጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ 497 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ገቢው ከዕቅዱ አንጻር የ91 ነጥብ 8 በመቶ አፈጻጸም እንዳለውም ነው ያነሱት፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅሟ ብሎም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እድገት እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን መሥራት መቻሉና ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ኢነርጂ የማግኘት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ወደ ኬንያ ሲቀርብ የነበረው ኃይል በሙከራ ሽያጭ ደረጃ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ግን ስምምነቱ በሚያስቀምጠው መሠረት 200 ሜጋ ዋት ኃይል ለኬንያ እየቀረበ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ይህም ከኃይል ሽያጭ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽዖ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ለደቡብ ሱዳንና ታንዛንያ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወደ ኬንያ የተዘረጋው መስመር እስከ 2 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማስተላለፍ አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህን መስመር በመጠቀምም ለታንዛንያ በቀላሉ ኃይል ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻልም ገልፀዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ለታንዛንያ ኃይል ለማቅረብ ድርድሮች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፤ ከደቡብ ሱዳን ጋርም የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ቴክኒካል ሥራዎች በባለሙያዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡