ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተገቢ ውክልና ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው-አቶ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት13/2017(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋማት (አይ ኤም ኤፍ) ተገቢውን ውክልና ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በተግባር ተጨባጭ ውጤት በሚያመጡ በባለብዙ ወገን የትብብር ማዕቀፎች ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምቀጥልም አስታውቀዋል።

አቶ ማሞ ከሲጂቲኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎች ታዳጊ አገራትም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተገቢውን ውክልና እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን ትብብር ላይ እየሰሩ ነው።

ኢትዮጵያም በርካታ በሁለትዮሽና በሌሎች ትብብሮች የምትፈጥራቸው ግንኙነቶች ብሄራዊ ጥቅሟን ታሳቢ አድርገው የሚመሰረቱ ናቸው ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባል ቢሆኑም፤ በድርጅቱ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ስለሌላቸው በምክር ቤቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተጽእኖ ሰለባ እንደሚሆኑም አቶ ማሞ አስረድተዋል።

የአይኤምኤፍ መስራች አገራት ከሌሎች የበለጠ ተጽእኖ የማሳደር አቅማቸውን ተጠቅመው የሚፈልጉትን ነገር እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ቃል ከመግባት ባሻገር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ጋር በትብብር መስራቱ አዋጪ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ማሞ አክለውም “ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ነባራዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከበፊቱ የተለየ በመሆኑ ለምትፈልገው የልማት መንገድ አጋዥ ከሚሆኑ አካላት ጋር በትብብር መስራቷ የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋታል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የመሰረተችው ግንኙነት አንዱን በሌላው አገር የመተካት ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ አስረድተዋል። 

የኢትዮጰያና ቻይና ግንኙነት በጋራ በመልማትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያነሱት አቶ ማሞ፤ ቻይና በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት በመስፋፋት፣ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፣ የልማት ፋይናንስ በማቅረብና የኢትዮጰያ የወጪ ምርቶች መዳረሻ በመሆን ሚናዋ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት አሁን ካለበት ደረጃ ይበልጥ እንዲያድግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ33 የአፍሪካ ሀገራት ከቀረጥ ነጻ (የዜሮ ታሪፍ) ማስገባት እንዲችሉ በ2024 በቻይና አፍሪካ የትብብር መድረክ (FOCAC) የመሪዎች ጉባኤ ላይ መግለጿ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በተግባር ተጨባጭ ውጤት በሚያመጡ በባለብዙ ወገን የትብብር ማዕቀፎች ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ  እንደምቀጥልም አቶ ማሞ አስታውቀዋል። 

አንድም የአፍሪካ አገር የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንደሌለው አንስተው፤ ይህም አሁን ያለውን የዓለም ምጣኔ ኃብታዊ ሥርዓት አያመለክቱም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአይኤምኤፍ ያላት ድርሻ እዚህግባ የሚባል ባለመሆኑ ይህን እውነታ ለመቀየርና ለልማቷ የሚያሰፈልገውን ሃብት ለማገኘት ያሉትን አማራጮች ሁሉ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑ በሩሲያ ካዛን በመካሄድ ላይ ያለው ጉባኤ የውይይት ጭብጦችም ልማት ላይ ያተኮሩ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በንጹህ ታዳሽ ኃይል አቅርቦት በስፋት መስራቷ በአካባቢ ጥበቃ ወደ መሪነት እንድትመጣና የብሪክስ አባል እንድትሆን ማስቻሉን አቶ ማሞ መግለጻቸውን ሲጂቲኤን በዘገባው አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከሊግ ኦፍ ኔሽንስ ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማትን ስትመሰርት መቆየቷን አቶ ማሞ አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ያለትን የዲፕሎማሲ ተሞክሮ ማሳያ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገንቢ ሚና እያሳረፈች መሆኑን አብራርተው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገራት የሚኖራትን ድምፅ የመሆን አስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።  

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉርና በቀጣናው ያላት የዲፕሎማሲ ሚና፣ የሕዝብ ብዛትና የምጣኔ ኃብት አቅም ድርሻ እንደሚታወቅ አብራርተው፣ እ.ኤ.አ. በ2040 እና በ2050 አፍሪካ ሩቡ የዓለም ሕዝብ መኖሪያ ስትሆን ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ደግሞ የአህጉሪቱ ቀዳሚ አገራት ሆነው እንደሚወጡ አስረድተዋ።

ኢትዮጵያ በንጹህ ታዳሽ ኃይል አቅርቦት በስፋት መስራቷ በአካባቢ ጥበቃ ወደ መሪነት እንድትመጣ በማድረግ የብሪክስ አባል እንድትሆን ማስቻሉን አቶ ማሞ ገልጸዋል ሲል ሲጂቲኤን በዘገባው ጠቅሷል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም