ቀጥታ፡

በተለያዩ ዘርፎች ችግሮችን የሚፈቱና ሥራን የሚያቀላጥፉ ፈጠራዎችን ይዘው ብቅ ያሉ ታዳጊዎች

በተለያዩ ዘርፎች ችግሮችን የሚፈቱና ሥራን የሚያቀላጥፉ ፈጠራዎችን ይዘው ብቅ ያሉ ታዳጊዎች።

በዓለም ላይ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ፉክክር በሚታይበት በዚህ ዘመን አገራት ምርታማነትን የሚጨምሩና በምጣኔ ኃብት ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የፈጠራ ውጤቶችን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተመራ ባለው ዓለም በሁሉም ዘርፍ ስኬታማና ተወዳዳሪ ለመሆን የምርምርና የፈጠራ ሥራ ለነገ የማይተው ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል።  

በኢትዮጵያም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መንግሥት ፈጠራዎችን በማበረታታት፣ የቴክኖሎጂና የዲጂታል አሠራሮችን በማስፋትና በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

በተለይም የታዳጊዎችን የፈጠራ ክህሎት በማበረታታት፣ በመደገፍና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ-ብዙ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤት እየታየባቸው ነው።

በዚህም መሠረት ታዳጊዎች በግብርና፣ በጤና፣ በኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች የተለያዩ ፈጠራዎችን በማበርከት ላይ ይገኛሉ። 

የታዳጊዎችን የፈጠራ ውጤት ለማበረታታትም በሒሳብ፣ ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ዘርፎች የተለየ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ማዕከላት ፈጠራቸውን እያዳበሩ ይገኛሉ።

ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ዘአማኑኤል ደረጄ እና ጓደኞቹ በውኃ ላይ የሚስተዋልን ቆሻሻ ለማስወገድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ፈጠራ በጥሩ ማሳያነት ይጠቀሳል።

የፈጠራ ውጤቱ ግድቦችን ጨምሮ በማንኛውም የውኃ ኃብት ላይ የሚከሰትን ቆሻሻ በመጥረግ ንፁህ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ዘአማኑኤል ያብራራል።


 

ከመቀሌ ቃላሚኖ አዳሪ ትምህርት ቤት ስቲም ማዕከል የ12ኛ ክፍል ተማሪ መሠረት ኪዳነማሪያም ደግሞ በግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋልን በሽታ ቀድሞ መለየት የሚያስችል ፈጠራ ይፋ አድርጋለች።

በግብርና ምርት ላይ የሚከሰቱና ምርታማነትን የሚቀንሱ ተባዮችና የሰብል በሽታዎች በየጊዜው የሚያደርሱትን ጉዳት በማየት ለፈጠራ እንዳነሳሳት ተናግራለች።

በዚህም መሠረት በግብርና ሰብሎች ላይ የሚስተዋልን በሽታ ቀድሞ በመለየት አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል የተሳካ ፈጠራ እውን ማድረጉን ጠቅሳለች።


 

ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዲናኦል እንቁ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በሕክምናው ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጥ ሮቦት ፈጥረዋል። 

ሮቦቱም ወረርሽኝ በሚከሰትበት አጋጣሚ ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ ለሕሙማን አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑን አስረድቷል።

የሕሙማንን የልብ ምትና የሙቀት መጠን በመለካት እንዲሁም ለሕክምና ባለሙያዎች የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶችን በማቅረብ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አብራርቷል።

በቀጣይም ታዳጊዎቹ በጤና፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ፈጠራዎችን   እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም