በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው 11 ሚሊየን ሄክታር መሬት 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ አየር ጸባይና ለም አፈር ባለቤት ነች።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሚሆኑ የግብርና ውጤቶችን በማምረት ሀገርንም፤ አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ፤ በ2016/17 ዓ.ም የመኸር ወቅት 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከ11 ሚሊየን ሄክታር በላይ በዘር መሸፈኑን ገልፀዋል።
አሁን ላይ ምርቱን ለመሰብሰብ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም የመሰብሰብ ሥራዎች መጀመራቸውን አንስተዋል።
ከዚህም ወደ 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በበጋ መስኖ በዘንድሮ ዓመት 4 ሚሊየን ሄክታር ስንዴ እንደሚሸፈን ጠቁመዋል።
ይህንንም በሙሉ አቅም ለማሳካት ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።
እስካሁንም የማሳ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ ወደ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።