ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ 100 ቀናት የተቋማት አፈጻጸም ግምገማ መካሄድ ጀመረ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ 100 ቀናት የሴክተር ተቋማት፣ የሪፎርምና ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈጻጸም ግምገማ መካሄድ ጀምሯል።

በግምገማው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፣  የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንዲሁም የፌደራል ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ግምገማውን ሲያስጀምሩ ኢትዮጵያ የሦስት ዓመት የመካከለኛ ዘመን ዕቅድና የሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተገበረች ነው ብለዋል።

የዚህ ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት አፈጻጸም በሚኒስትሮች ደረጃ መገምገሙን አንስተው፤ ዛሬም በፌደራል አስፈጻሚ ተቋማት አመራሮች ደረጃ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈጻጸም ግምገማ መጀመሩን ተናግረዋል። 

በሩብ ዓመቱ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መገባቱን ተከትሎ አስፈጻሚ ተቋማት አውዱን ተገንዝቦ የመሥራት ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል። 

ለየት ባለ መልኩ የደረስንበትን ደረጃና ቀጣይ የቤት ሥራዎች ላይ ያተኮረው ግምገማ በተሟላ መረጃ ለመሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል። 

የግምገማው ዋና ዋና ትኩረቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አሁናዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አዝማሚያዎች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው እንድምታ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አፈጻጸምና ዋና ዋና የኢኮኖሚና ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ቀጣይ ትኩረቶችን ማመላከት ላይ መሆኑን አንስተዋል። 

በማክሮ ማሻሻያ ትግበራው በሩብ ዓመቱ የገቢ አሰባሰብ መሻሻሉ፣ የልማት ፋይናንስ ዕድገት መመዝገቡ፣ የወጪ አስተዳደርና የዕዳ ጫና ማቃለል ላይ ውጤታማ ለውጦች ተስተውለዋል ነው ያሉት። 

የውጭ ምንዛሬ ተመን ገበያ መር መሆኑ በትይዩ ገበያ መናር ምክንያት ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ ለውጥ ማምጣቱን ገልፀዋል። 

በውጭ ምንዛሬ ግኝት ከሐዋላ፣ ከውጭ ንግድና ቀጥታ ኢንቨስትመንት የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ብለዋል። 


 

ብልሹ አሠራሮች እንዲስተካከሉ ውድድር እንዲጠናከር ትኩረት የተሰጠበትና ጠንክሮ የመሥራት ውጤት የታየበት ሩብ ዓመት እንደነበርም ገልፀዋል። 

በወጪ ንግድ በተለይም በቡና፣ በወርቅ በቁም እንስሳትና በጥራጥሬ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቅሰዋል። 

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግድ ተዋንያንን በማበረታታትና ኮንትሮባንድን በመቀነስ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል። 

በዓመቱ ለማስመዝገብ የታቀደውን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል አመላካች ውጤት በዘርፎች መገኘቱንም ተናግረዋል። 

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የያዝነውን ዓላማ ለማሳካት በትክክለኛ መንገድ ላይ ነን ብለዋል።

በመሆኑም በግምገማው የተሟላ መረጃና የጋራ መግባባት በመፍጠር የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም የሚያሳኩ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።


 

በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈጻጸምና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንድምታ ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል።

በማብራሪያቸውም በዓመቱ የታቀደውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ እንደሚቻል የሚያመላክቱ ውጤቶች ታይተዋል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም