ኢትዮጵያ ታምርት የኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ተጨባጭ አስተዋፅኦ ወደ ማበርከት እንዲሸጋገር አድርጎታል - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታምርት የኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ተጨባጭ አስተዋፅኦ ወደ ማበርከት እንዲሸጋገር አድርጎታል - አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ታምርት የኢንዱስትሪው ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ተጨባጭ አስተዋፅኦ ወደ ማበርከት እንዲሸጋገር ማድረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
መንግሥት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ከዚህም አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሁለት ዓመት በፊት ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ታምርት የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እና ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ አምራቾችን የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ በማሸጋገር ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲያበረክት ማድረጉን አመልክተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ንቅናቄው የብድር፣ የውጭ ምንዛሬ እና የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲሁም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉንም ነው የገለጹት።
የዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማደግ እና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ማሳያ እንደሆኑም መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።