የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽን የማስፋት ጉዳይ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል - የዘርፉ ሙያተኞች እና ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽን የማስፋት ጉዳይ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል - የዘርፉ ሙያተኞች እና ወጣቶች

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ስራ በትኩረት ሊሰራበት የዘርፉ ሙያተኞች እና ወጣቶች ገለጹ።
ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ ተሳታፊ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የስፖርት መሰረተ ልማት ማስፋፋትን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ፈታኝ ሁኔታ ቢኖርም የአህጉራዊው እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበርን (ፊፋ) መስፈርት ያሟሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በ46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ስታዲየሞችን እየገነባችና ያሉትን ደግሞ የማሻሻል ሥራን እያከናወነች መሆኑን አመልክተዋል።
የጋምቤላ ክልል ነዋሪዋ ወጣት ጋሻመኒ ኡሞድ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የመዝናኛ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸውን ገልጻለች።
መንግስት ወጣቱ ያለበት የስፖርትና የመዝናኛ ችግር እንዲፈታ እና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጻለች።
የሐረሪ ክልል የስፖርት ባለሙያ ወጣት አልዓዛር ገሰሰ በስፓርትና በስብዕና የዳበረ ዜጋን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋቱ ተግባር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብሏል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ አሰልጣኝ ተስፋዬ ያደታ ክልሉ ሳላዲን ሰኢድን እና አልማዝ አያናን የመሳሰሉ በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ሀገርን የወከሉ በርካታ ስመ ጥር ስፖርተኞች የተገኙበት ክልል መሆኑን ተናግሯል።
ይሁን እንጂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በስፋት ገንብቶ ሌሎች ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራቱ ረገድ ውስንነቶች መኖራቸው ጠቁመው፣ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብሏል።
በተለይም በክልሉ ከ10 ዓመት በፊት የተጀመረው የዘመናዊ ስታዲዮም ግንባታ ቢጠናቀቅ የስፖርቱን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፤ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የአፋር ክልል የስፖርት አደረጃጀትና ማዘውተሪያ ቦታዎች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ በርሄ እንዳሉት በክልሉ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አለመኖራቸው ብቻም ሳይሆን ያሉትም በተፈለገው ደረጃ የተደራጁ አደደሉም።
በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ያሉትን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ዘርፉን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የመንግስትና የባለሃብቶች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
ስፖርት በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት ዓይነተኛ ሚና ያለው ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሐረሪ ክልል የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ባለሙያ ኢንጂነር ሀዳ መሀመድ ናቸው።
ቢሮው ይህንን ታሳቢ በማድረግ ቀደም ሲል ለሌላ ስራ እንዲውሉ የተደረጉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በማስመለስና ያሉትንም የማጠናከር ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ታይዶር ቻምባንግ ክልሉ ለሁሉም የስፖርት ዓይነቶች የሚስማማ ተክለ-ቁመና ያላቸው ወጣቶች መገኛና ስመጥር ስፖርተኞች የወጡበትም ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ያለውን አቅም ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አለመስፋፋታቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ በጋምቤላ ከተማ በ2007 የዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ የተጀመረ ቢሆንም በአቅም ውስንነት ምክንያት ስራው መቋረጡን ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ የገንዝብ ምንጭ በማፈላለግ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ተወካዩ፣ ሌሎት የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ለማስፋፋትም በተቻለ መጠን ጥረት ይደረጋል ብለዋል።