በሶማሌ ክልል የአገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች አጀንዳዎች በማሰባሰብ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለኮሚሽኑ አስረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የአገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች አጀንዳዎች በማሰባሰብ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለኮሚሽኑ አስረከቡ
ጅግጅጋ ፤ጥቅምት 13/2017 (ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ለአገር ይበጃሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች በማሰባሰብ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ዛሬ ለኮሚሽኑ አስረከቡ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ አጠናቋል።
ተሳፊዎች በቆይታቸው ለአገር ይበጃሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች በማሰበሰብ በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት ዛሬ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል።
ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ በክልሉ ካለፈው ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አድገት ይበጃሉ ያሏቸውን ሃሳቦች በነፃነት በማዋጣት ረገድ መልካም ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎች ለህዝብና ለአገር ይጠቅማሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች በመለየትና በማሰባሰብ ረገድ ላሳዩት የነቃ ተሳትፎ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ምስጋና እንዳለው ተናግረዋል።
እንዲሁም በክልሉ ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ያለምንም ችግር በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ፣ የጎሳ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተባባሪ አካላት ሁሉ ኮሚሽኑ የላቀ ምስጋና እንዳለው ዋና ኮሚሽነር መስፍን ተናግረዋል።
እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ በጎ ፍቃደኞች እና የተለያዩ ተቋማትና የማህበረሰብ መሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ "ያሉባትን ችግሮች በውይይት የምትፈታ አገር" የሚለው ስም እንዲኖራትና ለአገር ዘላቂ ሰላም መጎልበት ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክት አስገንዝበዋል።
ተሳታፊዎች በቆይታቸው ለሀገር ዘላቂ ሰላም ይበጃሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች በማሰባሰብ እና በማደራጀት በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል።
ባለድርሻ አካላቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ምክክርም ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮችንም መርጠዋል።