መንግስት የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀትን ጨምሮ የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ ገለጹ።
አቶ ሀሰን ከቻይና ታንሹ ከተማ የመጡ የኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ለልዑካን ቡድኑ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ አማራጮች እና ምቹ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የቻይና የአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ኢንቨስትመንት ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
መንግስት ተስማሚ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በመቅረጽ እና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሟላ የመሰረተ ልማት በመዘርጋት የውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።