የኢትዮጵያና ኦስትሪያን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ኦስትሪያን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ኦስትሪያን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ተናገሩ።
የተለያዩ የኦስትሪያ- ኢትዮጵያ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ዕድሎችና ማበረታቻዎች ገለፃ ተደርጓል።
በዚሁ ሁነት ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፤ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ምቹነት እውን የሚያደርጉ የተለያዩ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አንስተዋል።
የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችን ጨምሮ በቅርቡ የተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዘርፉ ልማት መነቃቃት መፍጠራቸውን አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ የኢኮኖሚ መስኮች አሁን ላይ ክፍት መደረጋቸውን አንስተው፤ለአልሚ ባለሃብቶች ድጋፍና ማበረታቻዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያና ኦስትሪያ የኢንቨስትመንት ፎረም በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት የሚኖረውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና ኦስትሪያን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ይበልጥ ለማጠናከር ሰፋፊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታዎች እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል ከመሆኗ ባሻገር የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በሂደት ላይ መሆኗን አንስተው፤ይህም ለኢንቨስትመንት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ናፕ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያና ኦስትሪያ በሕዝብ ለሕዝብ፣በባህል እንዲሁም በትምህርት የረዥም ጊዜ የትብብር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በንግድና የኢኮኖሚ መስክ ያለው ትብብርም እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኦስትሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በትናንትናው እለት በተካሄደው የኢትዮ-ኦስትሪያ ቢዝነስ ፎረም ጎን ለጎን ኦስትሪያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ የከፈተችበት 60ኛ ዓመትም ታስቦ ውሏል።