የሌማት ትሩፋት የዜጎችን ሥርዓተ-ምግብ በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦት መፍጠር አስችሏል - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት የዜጎችን ሥርዓተ-ምግብ በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦት መፍጠር አስችሏል - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2017(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት የዜጎችን ሥርዓተ-ምግብ በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦትና ፍላጎትን በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ በሚያጋጥሟት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ዜጎቿ ለችግር ይዳረጉ እንደነበር ይታወቃል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በግብርና ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ከሚፈጥረው ችግር ለመላቀቅ የሚያስችሉ ሥራዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ ውስጥም የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር አንዱ ሲሆን፤ ዓላማውም የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥና ክብርን ማስጠበቅ ነው።
መርኃ-ግብሩ የኢትዮጵያን ደካማ የአምራችነት ታሪክ በመቀየር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የኢኮኖሚ እድገትን የማፋጠን ግብ የሰነቀ ሲሆን፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥም የሚታዩና ዓለም የመሰከረላቸው ውጤቶች መታየት ጀምረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት የዜጎችን ሥርዓተ-ምግብ በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦትና ፍላጎትን በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት በአርባ ምንጭ ከተማ ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት ለእንስሳትና ዓሳ ኃብት ምርታማነት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልፀዋል።
መንግሥት ለዘርፉ ዕድገት በሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል፣ በመኖ አቅርቦት፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎ፣ የዶሮና የዓሳ ጫጩት ሥርጭትን በማሳለጥ በዘርፉ ላይ እመርታዊ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።
ለአብነትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት ይፋ ከመደረጉ በፊት በዝርያ ማሻሻል ይዳቀል የነበረውን 500 ሺህ ላምና ጊደሮች ባለፈው ዓመት 2 ነጥብ 4 ሚሊየን በማዳቀል ዕድገት መመዝገቡን ገልፀዋል።
በዚህም ከላሞችና ጊደሮች ይገኝ የነበረውን የ5 ነጥብ 8 ቢሊየን ሊትር የወተት ምርት በማሳደግ ወደ 10 ቢሊየን ሊትር ወተት ማግኘት የተቻለበት መሆኑንም አብራርተዋል።
አርሶና አርብቶ አደሩ የአንድ ቀን ጫጩት እንዲያገኝ በማስቻል በተደረገው ስኬታማ የሥርጭት ሥራም በሥጋ ዶሮና በእንቁላል ምርታማነት ላይ የሚታይ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
በዶሮና እንቁላል ምርት የገበያ አቅርቦትና ፍላጎት ላይ የተሻለ እንዲሆን ማስቻሉን ገልፀዋል።
የጤና መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አንድ ሰው ካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲንና ቫይታሚን የመሳሰሉትን ንጥረ ነገሮች የያዙ የምግብ ተዋጽዖ ውጤቶችን መመገብ እንዳለበት ያሳውቃል።
በዚህም ለሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት በተሰጠው ትኩረት አርሶና አርብቶ አደሩን በቤተሰብ ደረጃ የአመጋገብ ሥርዓትን በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦትና ፍላጎት እንዲፈጠር ማድረጉን ገልፀዋል።