ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ያላቸውን የቆየ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ያላቸውን የቆየ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ያላቸውን የቆየ የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለገሰ ገረመው ከናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሳፊ ኦሉካዮዴ ኦላኒያን ጋር ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ረጅም ጊዜ የቆየ የሁለትዮሽ ትብብር እንዳላቸው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሁሉም መስኮች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች የፈረሟቸውን የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈጻሚነት ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ ሀገራቱ የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን በናይጄሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።