ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካና በአካባቢው ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ጉልህ ሚና አላት - የጀርመን ፖርላማ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካና በአካባቢው ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ጉልህ ሚና አላት - የጀርመን ፖርላማ አባላት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካና በአካባቢው ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ጉልህ ሚና እንዳላት የጀርመን ፖርላማ አባላት ገለጹ።
በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ሀገራት ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ከጀርመን ፖርላማ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ልዑካን ጋር ተካሂዷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን በሀገር ውስጥ እና በአካባቢው ለማስፈን እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በመተግበር ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ እና በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በርካታ ሥራዎችን ማከናወኗንም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመዋል።
ሰላም እና መረጋጋትን በውይይት ለማስፈን የበኩሏን እየተወጣች ያለችው ኢትዮጵያ በርካታ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይም ትገኛለች ብለዋል።
በዓለም ላይ የሚደረጉ ጦርነቶች የሀገራትን ዕድገት ወደ ኋላ የሚጎትቱ በመሆናቸው በውይይትና በንግግር መፍታት እንደሚገባ ነው ሰብሳቢው ያስገነዘቡት።
የጀርመን ፖርላማ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ጉልህ ሚና እንዳላት አመልክተዋል።
በአካባቢው ሀገራት ሰላምን ለማስፈንና ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል የሚደረጉ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።