ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሀገራዊ ጥቅሟን እና የጎረቤት ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስራዋን አጠናክራ ትቀጥላለች - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሀገራዊ ጥቅሟን እና የጎረቤት ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስራዋን አጠናክራ ትቀጥላለች - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሀገራዊ ጥቅሟንና የጎረቤት ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስራዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ሚኒስትሯ "የውጭ ግንኙነት እመርታ፤ ከገፅታ ግንባታ ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት" በሚል ርዕስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች አመራሮች ገለጻ አድርገዋል።
ገለጻውን ተከትሎ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጅነት በማውጣትና ያላትን አቅም በመጠቀም በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ እመርታ በማምጣት በዓለም መድረኮች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ከሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቱ ስራ የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቅሰው የብሪክስ አባል መሆኗ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮርና የልዕልና መር የውጭ ግንኙነት ፖሊስ የምትከተል መሆኗን አንስተው ከቅርብና ከሩቅ ካሉ ሀገራት ጋር በጋራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።
የሀገሪቱን ተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅም ለማሳደግ የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው።
ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች አባልነቷን በማጠናከር ድምጿ እንዲሰማ የማድረግ እንዲሁም አህጉራዊ በሆኑ ጉዳዮችም በንቃት መሳተፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ላይ ያተኮረ እንደሆነና ይህን እውን የሚያደርጉ ፖሊሲዎችን ከመቅረፅ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለአብነት አንስተው ግድቡ በኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ አልፎ በርካታ የጎረቤት ሀገራትን ማስተሳሰሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላት ትብብር የመደመር ዕሳቤ ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሆኑንም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የኢትዮጵያን ጥቅምና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት የድርሻውን እንዲወጣ ሚኒስትሯ ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።