ከ428 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
ከ428 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ባደረገው ክትትል 428 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታወቀ።
ከጥቅምት 1 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተያዙት እነዚህ የኮንትሮባንድ እቃዎች 134 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የገቢ፣ 294 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የወጭ መሆናቸውን አመልክቷል።
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ እቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ መድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እና የወጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል።
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ሀዋሳ፣ ሞያሌ እና ድሬድዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 29 ሚሊዮን፣ 28 ሚሊዮን እና 24 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዛቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ እና በበረራ የተያዙ መሆናውንም አስታውቋል።
የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 35 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና 12 ተሽከርካሪዎች መያዛቸውም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
የኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ሕብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣም የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል።