ቀጥታ፡

ዳያስፖራው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በፈጠራቸው አዳዲስ ዕድሎች ሀገሩን መጥቀም ይኖርበታል- የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፦ዳያስፖራው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በፈጠራቸው አዳዲስ ዕድሎች ሀገሩን እንዲጠቅም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ጥሪ አቀረቡ።

የባንኩ ገዥ በተገኙበትና ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች እና ሪፎርሙን ተከትሎ ስለተፈጠሩ አዳዲስ ዕድሎች ለተሳታፊዎች ገለጻ ተሰጥቷል።


 

በቅርቡ ወደ ትግበራ የገባው ገበያ-መር የውጭ ምንዛሪ ልውውጥ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ግኝት በእጅጉ የጨመረ መሆኑ ተገልጿል።

የዳያስፖራ ማህበረሰብ ያሉ ምቹ እድሎችን በመጠቀም የብልፅግና ጉዞው ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራ ዘርፉን በሚፈለገው መጠን እንዳይንቀሳቀስ አስረው ይዘውት የነበሩ አሰራሮች፣ ህጎችና ፖሊሲዎች መሰረታዊ በሚባል መልኩ የፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንኑ ተከትሎ የተፈጠሩ እድሎችን ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንዲጠቀሙበት ገልጸው ኢትዮጵያን በጋራ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል።

በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠባባቂ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር አስቴር ማሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም የተደረጉ ጥረቶች ውጤት ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ተሳታፊዎችም ውይይቱ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም በቀጣይ ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸው ውይይቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፎ ማድረጋቸውን በዋሺንግተን ዲሲ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም