ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን የላቀ አስተዋጽኦ አድርጋለች- ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጓን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቋል።

የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ፤ 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ በካፍ የአሰራር ስርዓት መሰረት ይታያል ሲሉ አረጋግጠዋል። 

በጉባዔው ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፤  ኢትዮጵያ የአፍሪካን እግር ኳስ ከመሰረቱት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስታውሰው ለዘርፉ እድገት አበርክቶዋን አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል። 

የካፍ ፕሬዝዳንት የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ ለአህጉሪቷ እግር ኳስ ጥሩ መሰረት ማኖራቸውን አስታውሰው ኢትዮጵያ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እግር ኳስ ወዳዶች ያሉባት ሀገር ስለመሆኗ አንስተዋል። 

በመሆኑም እ.አ.አ 2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ትክክለኛዋ ሀገር መሆኗን በማስረዳት ለዚህም አዳዲስ ዘመናዊ ስታዲየሞችን እየገነባችና የነበሩትንም እያደሰች ትገኛለች ብለዋል።

የካፍ መሥራች የሆነችው ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ብቃቱና ዝግጁነቱም አላት ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።


 

የዓለም እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፤ ለአፍሪካ እግር ኳስ ከምስረታው ጀምሮ አሁን ለደረሰበት እድገት የኢትዮጵያ ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት እና እድገት ፊፋ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የተጠናከረ ድጋፍ የሚያደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ከመስራችነት ጀምሮ የላቀ ሚና እንዳላት አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ያላቸው ስሜት እና ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑን እረዳለሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካን ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ በካፍ የአሰራር ስርዓት መሰረት ይታያል ሲሉ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ፤ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2029 የሚካሄደውን 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ በብቃትና በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።

አሁን ላይ 11 ስታዲየሞች በግንባታ እና በማሻሻያ ስራ መሆናቸውን ጠቅሰው ስታዲየሞቹ የካፍ እና ፊፋ መስፈርትን እንዲያሟሉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የተካሄደው 46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአፍሪካ እግር ኳስ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የካፍ መሥራች የሆነችው ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ያላትን ከፍተኛ ጉጉት በመጥቀስ ይፋዊ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወቃል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም