ቀጥታ፡

ሰልጣኞች በስልጠና ወቅት የሚያገኙትን አቅምና ክህሎት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማፋጠን ማዋል እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ/ዲላ/ሚዛን አማን፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፦ ሰልጣኞች በስልጠና ወቅት የሚያገኙትን አቅምና ክህሎት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማፋጠንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

"የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ ለሲዳማ ክልል እንዲሁም ለጌዴኦና ቤንች ሸኮ  ዞኖች በየደረጃው ላሉ አመራር አባላት የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በሀዋሳ፣ ዲላና በሚዛን አማን ከተሞች መሰጠት ተጀምሯል።


 

በሀዋሳ ከተማም መስጠት በተጀመረው ስልጠና የሲዳማ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት የፖለቲካ አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አስፋው ጎኔሶ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የብልጽግና ግቦችን ስኬታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ህልሞች ላይ ያተኮረ ነው። 

በተለይ ለልማት ግቦች ስኬታማነት አመራሩ ሰርቶ ከማሰራት ባለፈ ከፍ ያለ የልማት ህልሞች ያለው እንዲሆን ለማስቻል ታስቦ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። 

"አመራሩ ከኋላ ሳይሆን ከፊት ሆኖ ሰርቶ የሚያሰራና ሌሎች የሚከተሉት እንዲሆን ህልም ሊኖረው ይገባል" ያሉት አቶ አስፋው፤ በስነ ምግባር የታነጸ አገልጋይና ምሳሌ ሆኖ እንዲወጣ ስልጠናው ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስረድተዋል። 


 

በተያያዘ ዜና በዲላ ማዕከል መሰጠት በተጀመረው የሦስተኛው ዙር የመንግሥት አመራር አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ስልጠናው የመንግሥት አመራር አባላትን አቅም በመገንባት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ከዳር ለማድረስ ያለመ ነው።

አመራሩ በተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ላይ የጠራ አቋም ይዞ ለላቀ የህዝብ ተጠቃሚነት ተግቶ እንዲሰራ መሠረት የሚጥል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም አመራሩ በአቅም ግንባታ ስልጠና የሚያገኘውን ክህሎት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማፋጠንና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ስልጠናው ለውጡን ተከትሎ በዞኑ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ ስኬቶችን አመራሩ የማጽናት ሚናውን ለማሳደግ ይረዳል።

በተመሳሳይ ዜና በሚዛን አማን ከተማ በተዘጋጀ የስልጠና መድረኩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የቤንች ሸኮ ዞን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግፌ ኩድን እንደተናገሩት፤ ስልጠናው የእድገት ትልሞችን ከግብ ለማድረስ ሁሉም አመራር የተግባር ቁርጠኝነትን እንዲኖረው ያደርጋል።

ችግሮችን ፈጥኖ ከመፍታት አኳያ በአመራሩ ላይ የሚታየውን የአቅም ውስንነት ለመፍታት ለአቅም ግንባታ ሥራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።

አመራሩ አንድ አገርን የማገልገልና የማሳደግ ግብ ይዞ መስራት እንዲችል እና አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ ስልጠና መሆኑንም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም