ቀጥታ፡

የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲው የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲው የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ገለጹ።

ሀገር አቀፉን የሳይበር ደኅንነት ወር አስመልክቶ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲን ማስተግበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስተዳደሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፤ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ ቁልፍ መሠረተ-ልማት ደኅንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል ሰፊ ይዘት ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ ባለመሆኑ ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሁሉም ጥረትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በፖሊሲው ትግበራ ዙሪያ መከላከልን መሠረት ያደረገ የሰው ኃይል ብቃትን ማሳደግና ትብብርን ማጠናከር ተገቢመሆኑንምጠቅሰዋል።


 

የፖሊሲውን ይዘት ለውይይት ያቀረቡት የዋና ዳይሬክተሯ አማካሪ ፍቅረሥላሴ ጌታቸው፤ ፖሊሲው ዲጂታላይዜሽን እውን በማድረግ ሂደት የሳይበር ደኅንነት ዝግጁነትን ለመዘርጋት ያግዛል ብለዋል።

የፖሊሲው ዋና ዓላማ ሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት አቅምን በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ሲሆን፤ የሳይበር ደኅንነት ንቃተ-ህሊናንና አቅም ግንባታ ማሳደግ ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ሀገራዊ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲን ትብብር ለማጠናከር አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።


 

በመከላከያ ሚኒስቴር የሳይበር ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል አገር አስቻለ፤ በጸጥታው ዘርፍ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማጠናከር ፖሊሲው ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የዓለም አቀፍ የሕግ ግዴታዎች ዴስክ ቡድን መሪ ወንደሰን አበበ በበኩላቸው፤ በፖሊሲው መሠረት የፋይናንስ ዘርፉን ደኅንነት ለማስጠበቅ በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር "የቁልፍ መሠረተ-ልማት ደኅንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ በውይይትና የተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ በ2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም