ቀጥታ፡

በመርካቶ ሸማ ተራ የደረሰውን የእሳት አደጋ መንስኤ እየመረመርኩ ነው- የአዲስ አበባ ፖሊስ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦በመርካቶ ሸማ ተራ የደረሰውን የእሳት አደጋ መንስኤ ከፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት ምርመራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ትላንት ምሽት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሸማ ተራ ነባር የገበያ ማዕከልና በአካባቢው ባጋጠመ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ፖሊስ ገልጿል።

አደጋውን ለመከላከልና በአደጋው ምክንያት ሌላ ወንጀል እንዳይፈፀም እንዲሁም የአደጋ ተከላከይ ሰራተኞች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አስታውቋል።

የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሠላምና ፀጥታ መዋቅር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች ተቋማትም ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አደጋው እንዳይባባስ ጥረት ማድረጋቸው ተገልጿል።

አደጋውን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ 33 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን እና ከአደጋው ጋር በተያያዘ በ7 ሰዎች ቀላል በ2ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

አደጋውን ለመከለከል የፀጥታና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ላደረገው ድጋፍና ተባባሪነት ፖሊስም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ በደረው የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማውን ሃዘን ገልፆ ወደፊት በምርመራ የደረሰበትን ውጤት ለህዝብ እንሚያሳውቅም በማህበራዊ ትስስር ገጹ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም