በአገራዊ ምክክር ሂደት ለክልሉና ለአገር የሚበጁ አጀንዳዎችን ይዘን ቀርበናል - ኢዜአ አማርኛ
በአገራዊ ምክክር ሂደት ለክልሉና ለአገር የሚበጁ አጀንዳዎችን ይዘን ቀርበናል
ጅግጅጋ፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፦ በአገራዊ ምክክር ሂደት ለክልሉና ለአገር የሚበጁ አጀንዳዎችን ይዘው መቅረባቸውን በጅግጅጋ በአገራዊ የምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተናገሩ ።
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ማዕከል እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በመሳተፍ ላይ ካሉት ባለድርሻ አካላት መካከል በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኙበታል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንዳሉት፤ በአገራዊ የምክክር ሂደቱ ለክልሉና ለአገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን በማምጣት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እያደራጁ ነው።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ኢሴ ባና ሀጂ አቡበከር የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አገራዊ ምክክር መድረኩ መዘጋጀቱ አገራችን ካለችበት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መውጫ መንገድ አመላካች ነው።
ፓርቲያቸው መድረኩ ለአገር እና ለህዝብ የሚኖረውን ጠቀሜታ ተገንዝቦ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ መድረኩ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች መጥተው በመወያየት መፍትሄ እንደሚያገኙ ያላቸው እምነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ህዝብ ችግሮችን በመወያየት በባህልዊ መንገድ የመፍታት የቆየ ልምድ እንዳላው የጠቆሙት አቶ ኢሴ፤ አገራዊ ምክክር ሂደቱ ተሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አገር የሚገነባ ሀሳብ ይዘው ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
አቶ ነስረዲን አህመድ ገራድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሶማሌ ክልል ተወካይ በበኩላቸው፤ አገራዊ ምክክር መድረኩ ህዝቦች በጋራ የሚያደርጉት ውይይቶች ጠንካራ መሰረት ያለው አገር መንግስት ለመገንባት እንደሚያችል አስረድተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀሳብ ትግል መለያየት ቢኖራቸውም ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትና ህዝቡን ለመሻገር ተቀራርበው ለመወያየት እጅግ ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አምነው፤ ለምክክር መድረኩ ቅድሚያ ሰጥተው ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
የሶማሌ ዴሞክራቲክ ሃይሎች ህብረት ዋና ፀሃፊ አቶ አብዱራህማን አህመድ በበኩላቸው፤ "ፓርቲያቸው አገራዊ ምክክር መድረኩ የሁሉም ችግሮች መውጫ መንገድ አመላካች ነው" የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል በመካሄድ ላይ ባለው የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የክልል ምክር ቤት አባላትና የመንግስት ሰራተኞች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።