ቀጥታ፡

የኢትዮ- ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

 አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/ 2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ በኢትዮጵያ  የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ናፕ፣ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዲሁም የሁለቱ አገራት ትልልቅ ኩባንያዎች ተገኝተዋል።  

በፎረሙ ላይ ለተሳተፉ የኦስትሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስላሉት የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

የገንዘብ  ሚኒስትር ደኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፤ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለአልሚዎች ምቹ እንዲሆን በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በሂደቱ ቀደም ሲል የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስታውሰው በቅርቡም ተግባራዊ የተደረገውን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጠቅስዋል።  


 

ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ ዘርፎች አሁን ላይ ክፍት ስለመደረጋቸው ገልጸዋል።

የቢዝነስ ፎረሙ የሁለቱን አገራት የትብብር ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግም አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።  

በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ናፕ፤ የሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም ይበልጥ የሚያጠናክሩ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዋል።   

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለው የኢትዮ- ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከፎረሙ ጎን ለጎን ኦስትሪያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ የከፈተችበት 60ኛ ዓመት የሚታሰብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም