ቀጥታ፡

ለፍትሕ ሚኒስቴር የተቀናጀ የወንጀል መረጃ ማስተዳደሪያ ሥርዓት ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/ 2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ፍትሕ ሚኒስቴር የተቀናጀ የወንጀል መረጃ ማስተዳደሪያ ሥርዓት ለማልማት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር)  ተፈራርመዋል።

የውል ስምምነቱ ከወንጀል ጥቆማ እስከ ፍርድ ድረስ ያለውን የተቀናጀ የወንጀል መረጃ በዘመናዊ መልኩ በማስተዳደር  የዲጂታል ሥርዓትን ማልማት የሚያስችል ነው ተብሏል።

ይህም በፍትሕ ሥርዓቱ የአገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።

በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሞባይል መተግበሪያ እና የዲጂታል ቋት እንደሚያለማ ታውቋል።

ዲጂታል የመረጃ ሥርዓቱ አጋዥ የመልዕክት መለዋወጫ (smart assistance chatbot)  ያካተተ በመሆኑ ማህበረሰቡ የተቋሙን ድጋፍና አገልግሎት በዲጂታል አማራጭ በቀላሉ  እንዲያገኝ ያስችላል ነው የተባለው።

በ84 ሚሊዮን ብር የሚለማው የተቀናጀ የወንጀል መረጃ ማስተዳደሪያ ሥርዓቱ በአንድ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም