የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 11 ፓርቲዎችን ለጊዜው አገደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 11 ፓርቲዎችን ለጊዜው አገደ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/ 2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጠቅላላ ጉባዔ፣ በኦዲት እና በሴት አባላት አማካኝነት ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዱን አስታወቀ።
ቦርዱ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዳስታወቀው ፓርቲዎቹ የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት እና አገው ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ናቸው።
በፓርቲዎቹ ላይ የተሰጠው የዕግድ ውሳኔም ቦርዱ የተለየ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ለጊዜው ከማንኛውም ሕጋዊ እንቅስቃሴ ታቅበው እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው።
በመሆኑም ቦርዱ የሰጠውን የዕግድ ውሳኔ እስከሚያነሳ ድረስም ከላይ የተገለጹት ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው ጉባዔዎች ላይ ሊገኙ፣ ሊመርጡም ሆነ ሊመረጡ እንዲሁም በኮሚቴ አባልነት ሊያገለግሉ አይችሉም ተብሏል።
የጋራ ምክር ቤቱ የዕግድ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ፓርቲዎች ከማንኛውም የምክር ቤቱ ሥራዎች እና እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈሉ እንዲያደረግ ቦርዱ አሳስቧል።