የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የምርትና የአገልግሎት ጥራት የትኩረት ማዕከል ሊሆን ይገባል -ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የምርትና የአገልግሎት ጥራት የትኩረት ማዕከል ሊሆን ይገባል -ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የምርትና የአገልግሎት ጥራት የትኩረት ማዕከል ሊሆን ይገባል ሲሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት የ2017 ዓ.ም የዓለም የደረጃዎች ቀንን "በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ኢንዱስትሪዎችን፣ የፈጠራ ስራዎችንና መሰረተ ልማቶችን ማስፋት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
በዝግጅቱ የተገኙት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በተወሰዱ እርምጃዎች በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነቡ ካሉ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ሆናለች ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርትና አገልግሎቶችን ለማቅረብ ትልቅ የጥራት ማዕከል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምርትና የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ በ 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በቴክኖሎጂ የተደራጀ የጥራት ቁጥጥር መንደር እንዲገነባ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ጥራት የንግድና የተወዳዳሪነት አንኳር ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምርትና የአገልግሎት ጥራት ጉዳይ የትኩረት ማዕከል ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ከመንግስት ባሻገር አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ልዩ ልዩ ደረጃዎችን በማዘጋጀት ለአምራቾችና ተጠቃሚዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ደረጃዎች መዘጋጀታቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 350 የሚሆኑት አስገዳጅ ደረጃዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሚዘጋጁ ደረጃዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፉ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራን ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ይህም ለቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ አሰራር ወሳኝ ነው ብለዋል።