አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፡- ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ልዑክ ከአይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ ተሳትፈዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ በሚገኙ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲሁም ከአይ ኤም ኤፍ ጋር በቀጣይ ትኩረት ስለሚደረግባቸው ትብብሮች ዙሪያ መክረዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያን ዕድገት በተለይም ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለማጎልበት በሚከናወኑ ተግባራት የአይ ኤም ኤፍ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን በማንሳት ምስጋና አቅርበዋል።
በሀገሪቱ እየተተገበረ ስለሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ትግበራውም ኢኮኖሚውን ለማጠናከር፣ ለማዘመን እና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስፈን ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህም በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ ያለውን ጉድለት መቅረፍን ጨምሮ ለዘርፉ ዕድገት ሌሎች አዎንታዊ ሚናዎችን ያበረክታል ብለዋል፡፡
የአይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጭነት እየተተገበረ ያለውን ሀገር በቀል ኢኮኖሚ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በሀገሪቷ ሁሉን አቀፍ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ቁልፍ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ አክለውም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ እና ለዚህም አይ ኤም ኤፍ እውቅና መስጠቱ ገልጸው፤ ይህም ለሌሎች ሀገራት ጭምር በአርዓያነት ሊወሰድ የሚችል ስኬት ነው ብለዋል።
በመሆኑም አይ ኤም ኤፍ የማስተካከያ ወጪዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያን የለውጥ ጥረቶች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከርም ተስማምተዋል፡፡