የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነት ጥያቄ በካፍ የአሰራር ስርዓት ይታያል - የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነት ጥያቄ በካፍ የአሰራር ስርዓት ይታያል - የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነት ጥያቄ ካፍ ባለው የአሰራር ስርዓት እንደሚታይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ ገለጹ።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን(ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሲፔ እና ሌሎች የካፍ አመራሮች ጠቅላላ ጉባኤውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ታሪካዊ ሚና እንዳላት እና የካፍ መስራች አባል መሆኗን የካፍ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ትልቅ ሚና የተጫወተች ሀገር እንደሆነችም ነው ያመላከቱት።
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄዋን ያቀረበችው በትክክለኛው ጊዜ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ያላቸው ስሜት እና ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑን እረዳለሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሕዝቡን አንድ የሚያደርግ ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞች እና የስፖርት መሰረተ ልማቶችን እንዳስጎበኟቸውና ባዩት ነገር መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ካፍ ባሉት የአሰራር ስርዓቶች እንደሚታይ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የካፍን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ ማስተናገዷን ገልጸው የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት አድንቀዋል።
በጉባዔው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ እና የካፍ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የፊፋ ዋና ፀሐፊ ማትያስ ግራፍስትሮም፣ የካፍ አባል ሀገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና የቀጣናዊ እግር ኳስ ማህበራት ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም፣ የበጀት፣ የፋይናንስ፣ የኦዲት እና የተለያዩ የካፍ ኮሚቴዎች ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የጠቅላላ ጉባዔው ሚና፣ የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓመታዊ ስብሰባዎች እና የካፍ ኤክስፖን ጨምሮ በካፍ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የሚገኙ የተለያዩ አንቀጾች ላይም ማሻሻያ ተደርጓል።
የአፍሪካን እግር ኳስ ልማትና እድገት ማጠናከር፣ አፍሪካ በዓለም እግር ኳስ ያላትን ውጤታማነት ማሳደግ፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ፣ የካፍ አባል ሀገራት ለእግር ኳስ ልማት የሚመድቡትን የፋይናንስ መጠን ማሳደግ፣ ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሁም ብልሹ አሰራርን በማስወገድ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እና ዘረኝነትን መከላከል በመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ የተነሱ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው።