ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ቤት ናት - የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017 (ኢዜአ)፦ ለአፍሪካ አንድነት ትልቅ ሚና የተወጣችው ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ቤት ናት ሲሉ የዓለም እግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ገለጹ።

46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የዓለም እግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ምስረታ እና ለአፍሪካ አንድነት ትልቅ ሚና መጫወቷን ገልጸዋል።

"ሁሌም ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ የአፍሪካ ቤት እንዳለሁ ይሰማኛል" ያሉት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፥ ወደ ኢትዮጵያ በድጋሚ በመምጣታቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለአፍሪካ እግር ኳስ የሚበጁ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

ፊፋ ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት እና እድገት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ካፍ የእግር ኳስ ልማት በተለይም የታዳጊ እና ወጣቶች እግር ኳስ ልማት ላይ አበክሮ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘረኝነትን በመከላከል እና ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ በበኩላቸው ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት እና ልማት አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ካፍ ያስመዘገባቸው ውጤቶች የአባል አገራቱም ውጤት ናቸው ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት በዓለም እግር ኳስ ላይ ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸው፥ እ.አ.አ በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት የተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ መድረሷ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከእ.አ.አ 2026 አንስቶ እያንዳንዱ የካፍ አባል ሀገር ሴቶች፣ ታዳጊዎች እና ወጣቶችን ጨምሮ ለእግር ኳስ ልማት የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚያገኝበት ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ካፍ ብልሹ አሰራርን፣ ዘረኝነት እና ስፖርታዊ ጨዋነት ያልተከተሉ ተግባራትን እንደማይታገስና አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

የአፍሪካ አገራት ውድድሮችን ለማስተናገድ የካፍ እና ፊፋ መመዘኛ መስፈርቶችን ያሟሉ ስታዲየሞች ማሟላት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ መሰረት የጣለች አገር መሆኗን ገልጸው ከካፍ መስራች አገራት መካከል አንዷ ናት ብለዋል።

የአፍሪካ ዋንጫን ሶስት ጊዜ በማስተናገድ አንድ ጊዜ ዋንጫ ማንሳቷን አውስተው ይድነቃቸው ተሰማ የካፍ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫን ወደ አገር ቤት መመለስ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2029 የሚካሄደውን 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧን ገልጸው ለዚህም በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።

በአሁኑ ሰዓት 11 ስታዲየሞች በግንባታ እና በማሻሻያ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው ስታዲየሞቹ የካፍ እና ፊፋ መስፈርትን እንዲያሟሉ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአሁኑ ሰዓት የፋይናንስ የአፈጻጸምን ጨምሮ የተለያዩ ሪፖርቶችን በማዳመጥ ይገኛል።

ጉባዔው በአፍሪካ እግር ኳስ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎች ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም