ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የአካባቢ ልማትና የጤና መሠረት የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የአካባቢ ልማትና የጤናም መሠረት መሆኑን በዓለም ጤና ድርጅት የአካባቢ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ማሪያ ኔራ ገለጹ።

የዓለም ወቅታዊ ፈተና ሆነው ከመጡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የአየር ንብረት ለውጥና የወቅቶች መዛባት ሆኗል።

በዚህም ምክንያት ለድርቅ፣ ከልክ ያለፈ ዝናብና በረዶ እንዲሁም ለሰው ልጆች ጤና አስቸጋሪ የሆኑ ክስተቶች በስፋት እየተስተዋሉ መጥተዋል።

ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመፍታት የጋራ ጥረትና ልማት አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት የግል ጥረታቸውን በማከል ለዘላቂ መፍትሔ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በእስካሁኑ ልማትም የኢትዮጵያ ደን ከነበረበት ዝቅተኛ ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ በማደግ የሚታይ ለውጥ ተመዝግቦበታል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በዓለም ጤና ድርጅት የአካባቢ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ማሪያ ኔራ፤ በዘርፉ ልማት የኢትዮጵያ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የአካባቢ ልማትና የጤናም መሠረት መሆኑን አብራርተዋል። 

በተለይም የውኃ አካላትን በመጠበቅ የውኃ ወለድ በሽታዎችን ክስተት ለመቀነስና በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን አብራርተዋል።  

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ከራሷም ባለፈ ለዓለም አቀፋዊ ትርጉም ያለው መሆኑንም ነው ዳይሬክተሯ ያነሱት።

በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የእናቶችና ህፃናትን ሞት መቀነስን ጨምሮ አጠቃላይ የዜጎቿን ጤና ለመጠበቅ የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ ድርጅታቸው ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም