ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲን በመተግበር ቁልፍ መሰረተ ልማትን ለማስጠበቅ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲን በመተግበር ቁልፍ መሰረተ ልማትን ለማስጠበቅ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲን በመተግበር ቁልፍ መሰረተ ልማትን ለማስጠበቅ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትግስት ሃሚድ ተናገሩ።
አስተዳደሩ 5ኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክቶ "ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲና የባለድርሻ አካላት ሚና" በሚል ውይይት እያካሄደ ነው።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትግስት ሃሚድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ቁልፍ መሰረተ ልማት ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል ሰፊ ይዘት ያለው ነው።
የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የአንድ ተቋም ባለመሆኑ ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ የአገርን የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የድርሻቸውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በፖሊሲው ትግበራ መከላከል ላይ ያተኮረ የሰው ሃይል ብቃትን ማሳደግና ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ዲጅታላይዜሽንን እውን ለማድረግና እየጨመሩ የመጡ የሳይበር ደህንነትን ለመቀነስ አገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲን ማውጣት ማስፈለጉ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ እያከናወነች ላለው ተግባር ትልቅ ፋይዳ ያለው ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ በ2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።
የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊናን ማሳደግ፣ የሳይበር ደህንነት አቅም ግንባታ ማሳደግን ጨምሮ ሰባት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ፖሊሲው በውስጡ ይዟል።
በውይይቱ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ይዘት ላይ ገለጻ ተደርጎ ቀጣይ ትግበራው ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
የሳይበር ወር በጥቅምት ወር በአለም አቀፍ ደረጃ ስለ ሳይበር ደህንነት ግንዛቤን ለማሳደግ የሚካሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መርሃ ግብር ነው።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው 5ኛው አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወርም "የቁልፍ መሰረተ-ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉአላዊነት" በሚል በውይይትና በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።