በተባይ አማካኝነት የሚከሰተውን የማንጎ በሽታን ለመከላከል የተከናወኑ የሥነ ህይወት ምርምር ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተባይ አማካኝነት የሚከሰተውን የማንጎ በሽታን ለመከላከል የተከናወኑ የሥነ ህይወት ምርምር ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው
አሶሳ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ በተባይ አማካኝነት የሚከሰተውን የማንጎ በሽታን ለመከላከል የተከናወኑ የሥነ ህይወት ምርምር ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተባይ አማካኝነት የሚከሰተውን የማንጎ በሽታን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ የሥነ ህይወት ምርምር ስራዎች ያመጡትን ለውጥ በመስክ ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የማንጎ ተባይ የማንጎ ምርት እንዲቀነስ እና የአምራቾችን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጎዳ የሚያደርግ ነው።
ኢንስቲትዩቱ በተባይ ምክንያት የሚከሰተውን የማንጎ በሽታን ለመከላከል በአገር አቀፍ ደረጃ የሥነ ህይወት ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በአሶሳ እና አርባምንጭ ላይ የተደረጉት ሙከራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
የማንጎ ቅጠልን ኬሚካል በመርጨት እና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ቆርጦ በመቀጠል(grafting) የበሽታውን ስርጭት መከላከል የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
በምርምሩ እንደ መፍትሔ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በጉንደላ ማዳቀል ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በማከል።
ዳይሬክተሩ አክለውም እስከአሁን በተሰሩት የምርምር ስራዎች በሽታውን በቀጣይነትም ለመቆጣጠር የሚያስችል የምርምር ውጤት ይፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ኦፍገኣ ጅራታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የማንጎ ዛፍ ከግዝፈቱ ጋር በተያያዘ ኬሚካል ለመርጨት ትልቅ ፈተና መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም የተጠቃውን ማንጎ ቆርጦ በተሻሻለ ዝርያ መተካት አንዱ አማራጭ እንደሆነ ገልፀው፤ ይህም አርሶ አደሩ መቆጣጠር እንዲችል እና ኬሚካሉን ለመርጨት ያግዛል ብለዋል።
በአርባምንጭ አካባቢ የተሞከረው ማንጎን የማዳቀል ስራ ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ለፍሬ መብቃቱንም ተመራማሪ ኦፍገኣ(ዶ/ር) ጠቅሰዋል።
የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ደስታ በቀለም ማዕከሉ የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ገልፀዋል።
ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የማንጎ ተባይን እና አቀንጭራን ለመቆጣጠር የሚያስችል የምርምር ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጉብኝታቸው የተመለከቱትና በምርምር እየተሄደበት ያለው የማንጎ ተባይ መከላከል የምርምር ሥራዎች ጥሩ ተስፋ እያሳየ መሆኑን አንስተው፤ በዚህ ረገድ ውጤታማ ተግባራቱን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅና በሰፊው እንዲተገበር ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በመስክ ምልከታው የኢትዮጵያ ባዮና ኢመርጂን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ እና የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።