የፕሪሚየር ሊጉ የአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ የአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዶ ቡድኑ በሁለት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባካሄዳቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በሶስቱ ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ጎል ብቻ አስተናግዷል።
በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ በስድስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ያደርጋል።
በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመራው ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል።
በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦች ተቆጥረውበት በስድስት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ በሊጉ ባከናወናቸው ሁለት ጨዋታዎች አቻ በመውጣት በሁለት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።