በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው የካፍ ወዳጅነት ጨዋታ ከውድድር ባሻገር ለአገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው - ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው የካፍ ወዳጅነት ጨዋታ ከውድድር ባሻገር ለአገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው - ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው የካፍ ወዳጅነት ጨዋታ ከውድድር ባሻገር ለአገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ የተሳተፉበት የካፍ የወዳጅነት የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።
በውድድሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የቀድሞ ኮከብ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋቾች ተሳትፈዋል።
ከእነዚህም መካከል የአፍሪካ የቀድሞ ኮከቦቹ ሳሙኤል ኤቶ፣ ኦኮቻ፣ አልሃጂ ዲዩፍ፣ ካሉሻ ቡዋሊያ፣ ኢትዮጵያውያኑ ሳላዲን ሰኢድ፣ አዳነ ግርማና ሌሎች የቀድሞ ኮከቦች ተጫውተዋል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት፤ 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው የካፍ የወዳጅነት ጨዋታም፥ ከእግር ኳስ ጨዋታ ባሻገር ለስፖርት ዲፕሎማሲ መጠናከር ብሎም ወዳጅነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ በማቅረብ የሚጠበቅባትን እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ ዛሬ ጠዋት በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የአደይ አበባ ስታዲየምን መጎብኘታቸው ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ዝግጅት ለማሳየት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
በወዳጅነት ጨዋታው ላይ ከተሳተፉት መካከል የዛምቢያ የቀድሞ ኮከብ ካሉሻ ቡዋሊያ በአዲስ አበባ በመገኘት የወዳጅነት ጨዋታ በማድረጉ መደሰቱን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረገለት አቀባበል አመስግኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ በጨዋታው መሳተፋቸው አስገራሚ ድባብን መፍጠሩን ጠቅሷል።
ሴኔጋላዊው የቀድሞ ኮከብ አልሃጂ ዲዩፍ በበኩሉ ኢትዮጵያ በቀጣይ የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ላይ ጥሩ ነገር እንደምትፈጥር ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ ኮከቦች ውስጥም ሳላዲን ሰኢድ እና አዳነ ግርማ በሰጡት አስተያየት የቀድሞ የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮከቦች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
የቀድሞ የአፍሪካ ኮከቦች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከካፍ አመራሮች ጋር ያደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ለኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች አርዓያ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲገነቡ ማድረጋቸው ይታወቃል።
46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባዔ ነገ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።