አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የኢትዮጵያን ብልጽግና በሚያሳካ መልኩ የሚተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የኢትዮጵያን ብልጽግና በሚያሳካ መልኩ የሚተገበር ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦ አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚን የመሪነት ሚና በማሳለጥ የኢትዮጵያን የብልጽግና ርዕይ በሚያሳካ መልኩ የሚተገበር መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) አስታወቁ።
የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮዎችና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የትውውቅ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
በዚሁ መድረክ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለሀገራዊ ዕድገት የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
በአረንጓዴ አሻራና በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ሥራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በቂ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅኦ ምርት ለገበያ እንዲቀርብ ማስቻላቸውን ገልጸዋል።
ፖሊሲው በዘርፉ እየተመዘገበ የሚገኘውን ስኬት ለማሳለጥ ዓይነተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።
በተለይም የግብርና ባንክ በማቋቋም ጭምር አርሶና አርብቶ አደሩ መሬትና የተፈጥሮ ኃብቱን በማስያዝ የገንዘብ ብድር አገልግሎት የሚያገኝበት ዕድል እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የገጠር ግብርናን መዋቅራዊ ሽግግር በማሳለጥ የኢትዮጵያን የብልጽግና ርዕይ ለማሳካት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑንም አብራርተዋል።
ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ አዋጅና ሌሎች መመሪያዎች በማዘጋጀት የገጠር ግብርና ሽግግርን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ፖሊሲው የውል እርሻ ልማት፣ የዘርና የእንስሳት ጤና አዋጆችን ተግባራዊ በማድረግ በሰብል፣ በእንስሳትና የተፈጥሮ ሃብት ምርታማነት ላይ ዘመናዊ የግብርና ሥርዓትን መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ በኩል በ2016/17 የመኸር ወቅት 20 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት በ20 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የገበያ ፍላጎትን የሚመልስ አቅርቦት መፍጠር እንዲቻል በዘር የተሸፈነውን ሰብል በተገቢው መንገድ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለ2017/18 የምርት ዘመን 24 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ የግዥና የማጓጓዝ ሂደት መጀመሩን ጠቁመዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ተሟላ ትግበራ መግባቱ የቁም እንስሳት ህገ-ወጥ የንግድ ሥርዓትን መስመር በማስያዝ አርሶና አርብቶ አደሩን ከእንስሳት ንግድ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሰረት በ2030 ዓ.ም የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር በማረጋገጥ በገጠር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ለሀገር ብልጽግና ጉልህ ሚና የሚጫወት ሆኖ የማየት ርዕይ ተይዟል።
ነባሩ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከ20 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየ ሲሆን ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም የተሻሻለው ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።